ነፃ የኦሮምያ መንግስት ወይም እውነተኛ የክልል ፌዴሬሽን

የትኛው የፖለቲካ ግብ ለኦሮሞ ሕዝብ ይበጃል?

በብርሃኑ ሁንዴ

ይህ ጥያቄ በጣም ከባድና መልሱም አከራካሪ እንደሚሆን የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ይሁን እንጂ የትኛው የፖለቲካ ግብ ለኦሮሞ ሕዝብ የተሻለ እንደሚሆን የሚወስኑ ብዙ ጉዳዮች አሉ። ስለሆነም ባጭሩ ሊገለፅ የሚችል ጉዳይ አይደለም። ትልቁ አከራካሪና ሊያስማማም የማይችል ጉዳይ የኦሮሞን ሕዝባዊ ብሔራዊ ጥያቄን እንዴት እንደምናይ እና እንደምንገልፅ ነው። በተጨማሪ ደግሞ የኢትዮጵያን አፈጣጠርና ባሕሪዋን እንዴት እንደምንወስድና እንደምናብራራ ነው። አንዳንድ ሰዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ኢምፓየር ነችና፤ አንድ ኢምፓየር ደግሞ ወደ ዲሞክራሲነት መለወጥ ስለማይችል የግድ የሕዝቦቿ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተረጋግጦ የሀገሪትዋ የወደፊት ዕጣ መወሰን ይኖርበታል ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ሀገሪቷ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከተቀየረች የሕዝቦቿ ጥያቄ ሊመለስ ስለሚችል የግድ የየሀገሮች ነፃ መንግስት ማቋቋም አስፈላጊ አይሆንም ይላሉ።

ታሪክን የሚመለከት ስፋቱንና ጥልቀቱን ለታሪክ ፀሃፊውች ወይም ለታሪክ ባለሙያዎች በመተው፤ ነገር ገን ብዙ ነገሮች ማስረጃ ሊሆኑ እንደሚችሉት፣ የኢትዮጵያ አፈጣጠርና ባሕርይዋ በግልፅ የሚያሳዩት ይህቺ ሀገር ኢምፓየር አንደሆነች ነው። ይህ ከተባለ ደግሞ ይህቺ ሀገር ዲሞክራሲ ልሰፍንባት ስለማይችል፣ የሀገሪቷ የወደፊት ዕጣ ፋንታ በሕዝቦች ውሳኔ መረጋገጥ አለበት ወደሚለው ድምዳሜ ሊወስደን ይችላል ማለት ነው። ይሁን እንጂ አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ይህን ግብ ብመኝም፣ የሕዝብ ውሳኔ የኦሮምያ ነፃ መንግስት መመስረት ይሆናል ብለው ከወዲሁ መናገር ያስቸግራል። በሌላ በኩል ደግሞ ዲሞክራሲ የገዳ ስርዓት መገለጫ በመሆኑና ለኦሮሞ ሕዝብ ባሕሉም ቢሆንም፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ ከተነሳ፣ ሀገሮች የራሳቸው ነፃ መንግስት ስላቋቋሙ የዲሞክራሲ ሀገር ሆነዋል ማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ ለኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲ ጥያቄ ውስጥ መግባትም የለበትም።

በዚህች ፅሑፍ ርዕስ ላይ ወደ ተነሳው ጥያቄ ስንመለስ፣ የትኛው የፖለቲካ ግብ ለኦሮሞ ሕዝብ ይበጃል? የሚለው የሕዝቡ ውሳኔ ስለሚሆን፣ ይህንን ለሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ እተዋለሁ። የምበጀውን የሚወስነው ሕዝብ ነውና። እውነት እንናገር ከተባለ የራስ ነፃ ሀገር ተመስረቶ ማየትን የሚጠላ ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን ይህን ለማግኘት ምን ያህል መስዋዕት እንድሚጠይቅና ያሉት ሁኔታዎች ደግሞ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆኑ መረዳት አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ መስዋዕትን በተመለከተ ኢትዮጵያን ዲሞክራሳዊ ለማድረግ የጠየቀውም ሆነ የሚጠይቀው መስዋዕት ነፃ ሀገርን ለመመስረት ከሚጠይቀው ያነሰ አይሆንም ብለው የሚከራከሩ ሊኖሩ እንደሚችሉ አምናለሁ። ይሁን እንጂ በዚህች ምድር ላይ የማይቻል ነገር ባይኖርም፣ ነፃ ሀገር የመገንባቱ ፈተና እጅግ በጣም ከባድ እንደሚሆን የማይታበል ሀቅ ይመስለኛል።

ነፃይቷን ኦሮምያ ማየት የአብዛኛው ኦሮሞ ምኞት ቢሆንም፣ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት  ወይም እውነተኛ ፌዴሬሺን በኢትዮጵያ መረጋገጥ ከቻለ ለኦሮሞ ይጠቅማል እንጂ ሊጎዳ አይችልም የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን ይህ እውነተኛ ፌዴራሊዝም የኦሮሞን የሀገር ባለቤትነት (Abbaabiyummaa Oromoo) የሚያረጋግጥ ማለትም ኦሮሞ በሀገሩ የቀዬው፣ የመሬቱ፣ የንብረቱና የአስተዳደሩ ባለቤት ሆኖ፤ ያለ ምንም ውጫዊ ተፅዕኖ ክልሉን ማስተዳደርና ኢትዮጵያን ደግሞ በድርሻው መሰረት በጋራ ማስተዳደር ከቻለ ሊጎዳ አይችልም ማለት ነው። በዚህ ፌዴራሊዚም ውስጥ ግን ኢትዮጵያ ኦሮሞን እንደ ባዕድ የምታስተናግድ፣ ለኦሮሞ የማትቆረቆር የእንጀራ እናት ሳትሆን፣ ለኦሮሞም ሆነ ለሁሉም ሕዝቦቿ እውነተኛ እናት ሆና በአዲስ መልክ ስትመሰረት ብቻ ነው። ይህንን ቅድመ ሁኔታ የሚያሟላ ፌዴራሊዚም ወይንም ፌዴሬሽን መገንባት የማይችል ከሆነ ግን ያለው አማራጭ የራስን ነፃ ሀገር ማለትም የገዳ ሀገር የሆነች ”ዲሞክራሳዊት ሪፓብልክ ኦሮምያን” መገንባት የግድ ይሆናል ማለት ነው። ከንግዲህ በኋላ የኦሮሞ ሕዝብ የሚሰቃይባት ኢትዮጵያ ልትኖር እንደማትችል ጠላትም ሆነ ዘመድ መረዳት አለበት።

የፌዴራሊዝም ጥያቄ ካተነሳ ደግሞ፣ ፌዴራሊዝም ብዙ መልክ ስላለው ምን ዓይነት ፌዴራሊዝም መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል። የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ ባልሆንም፣ እንደ እኔ አመለካከት አሁን ያለው በክልሎች ላይ የተመሰረት ፌዴሬሽን በብዙ መልኩ ሲታይ ለዚህች ሀገር ጥሩ አማራጭ ይመስለኛል። ይህንን ሊቀበሉ የማይችሉ ኃይሎች አንዳሉ ቢታወቅም፤  ወደዱም ጠሉ የዚህ ዓይነት ፌዴሬሽን ባብዛኛው የሀገሪቷ ሕዝቦች ተቀባይነት አንዳለው ማመን አለባቸው።

በነገራችን ላይ አንድ ወቅት በFace Book ላይ አንድ አጭር ፅሁፍ በእንግሊዝኛ አቅርቤ ነበር። በዚያች ፅሁፍ ውስጥ ባሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች እንደ ትግላቸው ዓላማ በአምስት ቡድን (group) ከፍዬ ለማየት ሞክሬ ነበር።

  • ፩) ሩቅ ግራ (far left) እነዚህ የብሔር ነፃ አውጪ ድርጅቶች ወይም የነፃነት ግንባሮች ሲሆኑ ለሕዝቦች የራስ ዕድል በራስ የመውስን መብት የሚታገሉ ኃይሎች፤
  • ፪) መካከለኛ ግራ (middle left) እነዚህ እውነተኛ ፌዴሬሽን ከተቋቋመ የሕዝቦች ጥያቄ ሊመለስ ይችላል ብለው የሚያምኑ ኃይሎች፤
  • ፫) መካከለኛ (middle) አሁን ያለውን የተዛባ የፌዴራሊዝም ስርዓትን እንዳለ ማቆየት የሚፈለጉ ኃይሎች፤
  • ፬) መካከለኛ ቀኝ (middle right) እነዚህ ኃይሎች ምናልባት በፌዴራሊዚም ስርዓት የሚያምኑ ነገር ገን በክልሎች ላይ የተመሰረተውን ፌዴሬሽን የማይቀበሉ ኃይሎች፤
  • ፭) ሩቅ ቀኝ (far right) እነዚህ ኃይሎች የድሮውን ስርዓት ለመመለስ የሚያስቡ ኃይሎች ናቸው

እንግዲህ እነዚህ የተለያዩ እንዲያውም አብረው መሄድ የማይችሉትን የፖለቲካ ዓላማ አንግበው የተነሱትን አቀራርቦ አንድ የጋራ ዓላማ ላይ ለማስማማት ያለው ዕድል በጣም ትንሽ ይሆናል በዬ አስባለሁ። እንደ እኔ አስተሳሰብ ግን ከወቅቱም ሁኔታና ከሀገሪቷም ችግሮች አንፃር ሲታይ አማራጭ የጋራ ግብ ሊሆን የሚችለው አሁን ባለው፣ በክልሎች ላይ የተመሰረተ ነገር ግን እውነተኛ ፌዴሬሽን ቢረጋገጥ ለሁሉም ባይሆንም ለአብዛኛው በይበልጥ የተሻላ አማራጭ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ይህ እንግዲህ የፖለቲካ ኃይሎቹን ለማቀራረብ ሊረዳ ይችላል ከሚል አንፃር ነው። ያም ሆነ ይህ የማጨረሻ ውሳኔም ሆነ ድል ግን የሰፊው ሕዝብ ነው።

Leave a comment.

Your email address will not be published. Required fields are marked*

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.