የኦሮሞ ሕዝብ አንገብጋቢ ችግሮችና የኦህዲድ (OPDO) ትልቅ ፈተና

በአቶ ለማ መገርሳ እንደ ማር በሚጣፍጡት አባባሎች በስተጀርባ ምንድነው ያለው?

በብርሃኑ ሁንዴ

ከሁለት ዓመት በላይ የቆየና አሁንም እየተካሄደ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ (#OromoProtest) የተፈለገውን ግብ ባይደርስም ብዙ ጫናዎችን ያመጣ ይመስላል። ከነዚህም ጫናዎች ውስጥ አንዱ በኦሆዲድ (OPDO) ላይ የሚታይ ሲሆን፤ ቢያንስ የኦሮሞን ብሔርተኝነት (Sabboonummaa Oromoo) እና ኦሮሞነትን (Oromummaa) የሚያንፃባርቁ አባባሎችን የሚናገር አዲስ አመራር በኦህዲድ ዉስጥ መታየት ነው። የዚህ የኦህዲድ አዲሱ አመራር ዋና ተዋናኝ የሆኑት ደግሞ የኦሮምያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ናቸው። የአቶ ለማ አነጋገር ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን ኦሮሞ ያልሆኑትን እንኳን እጅግ የሚስብ ነው። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ለኔ ግልፅ ያልሆነልኝ ነገር አለ። ይህንንም እንደሚከተለው ለማብራራት እሞክራለሁ።  ለማብራሪያው መግብያ እንዲሆን አንድ ጥያቄ ማንሳት እፈልጋለሁ።

ለኦህዲድ አዲሱ አመራር በተለይም የአቶ ለማ እንደዚህ መናገር መንስዔው ምንድነው?

አኔ እዚህ ላይ እንደ ዋናነት የማስበው የኦሮሞ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እየጠነከረ በመምጣቱ፤ ወደውም ይሁን ተገደው ለለውጥ የተነሳሱ ይመስላል። እዚህ ላይ ለለውጥ የተነሳሱ የሚለው በጥንቃቄ መታየትን ይጠይቃል። እስቲ “ወደውም ይሁን ተገደው” የሚለውን ሀረግ ለማብራራት ልሞክር። 1) በመጀመሪያ የኦህዲድን አመሰራረትና አሰራር መሰረት አድርገን ካየን “ተገደው”  የሚለው ቃል ራሱ በሁለት መንገድ ሊገለፅ ይችላል።

በቅድሚያ የማይካድ ሀቅ ኦህዲድ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ነፃ የሆነ ድርጅት አይደለም። በዚህ ላይ ደግሞ የኢህአዲግ አንዱ አባል ድርጅት ነው። በመሆኑም ከውጫዊ ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ በራሱ ውሳኔ ሲሰራ የታየበት ጊዜም ያለ አይመስለኝም። እናም የተወሰነ ተልዕኮ አለው ብዬ እገምታለሁ። እንግዲህ ተገደው ወደ ሚለው ስንመለስ ባጭሩ ለመግለፅ፥

  1. A) የኦሮሞ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለሕወሃት/ኢህአዲግ ስጋት ስለፈጠረ፤ በኦህዲድ በኩል ሕዝቡን ለማረጋጋት ተብሎ በአዲሱ አመራር በኩል የብሔርተኝነትን አንጋገር እንደ ስልት በመጠቀም እንቅስቃሴውን ለማቀዝቀዝ የተደረግ የፖለቲካ ዘዴ ሊሁን ይችላል ብዬ አስባለሁ።
  2. B) ሌላው ተገደው የሚለውን የሚገልፅ ግምት፣ የኦሮሞ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በጣም ተጠናክሮ እስከ መንግስት ለውጥ ድረስ የሚሄድ ከሆነ፣ ለኦህዲድም እጅግ አስጊ ስለሚሆን፣ ከሚከተለው ተጠያቂነት (የታሪክ ተጠያቂነት እንዳለ ሆኖ) ራሳቸውን ከወዲሁ ለማዳን ሲባል ወደ ሕዝባቸው ተመልሰው የሚቻላቸውን ለማድረግ የተገደዱ ሊሆን ይችላል።

2) ወደው ሊሆን ይችላል የሚለው ግምት አሁንም ከሕዝቡ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው። አንድ ከታሪክም አንፃር ማየትና መገንዘብ ያለብን ጉዳይ ኦህዲድ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጥንካሬና ድክመት የተወሰነ ወይንም የሚወሰን ድርጅት ነው። ምን ማለቴ ነው? ኦህዲድ ሳይመሰረት በፊት ኦነግ በወቅቱ አንዱ ጠንካራ ኃይል በመሆኑ ይህን ለማዳከም ከተቻለ ለማጥፋት ተብሎ ኦህዲድ በሴራ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ኦነግ ከሽግግር መንግስት ተገፍቶ ሲወጣ ሌላ የሚያሰጋቸው ኃይል ባለመኖሩ፤ ኦህዲድ የተመሰረትለትን ዓላማ በሚገባ ከግብ ለማድረስ ተልዕኮውን ሲያሳካ ቆይቷል።

በነገራችን ላይ የኦነግ መጠናከር የኦህዲድ መጠናከር እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ይህ የሚሆነው ደግሞ ወይ ጠንካራውን ኦነግ ለመጣል ወይንም ደግሞ ተፎካካሪ ሆኖ ለመስራት ሲባል ኦህዲድም ይጠናከራል ማለት ነው። ነገር ግን በምንም ምክንያት ይሁን የኦነግ እየተዳከመ መሄድና በቦታው ግን የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መምጣት፣ አንድ ሌላ ዕድል ፈጠረ። በዚህ በተፈጠረው ዕድል ለመጠቀም የሕዝባችን ችግርና ስቃይ የሚሰማቸው የኦህዲድ ዓባል የሆኑት የኦሮሞ ብሔርተኞች ለሕዝባቸው ለመስራት ብለው ወደው ብቅ በቅ ያሉ ይመስላል።

እንግዲህ የነ አቶ ለማ መገርሳ አዲሱ አመራር ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ግምቶች በየትኛው ላይ ተመስርተው አንደሆነ አሁን ማወቅ ያስቸግራል። ያም ሆነ ይህ ወደውም ይሁን ተገደው በቀላሉ መውጣት በማይችሉበት ትልቅ ፈተና ዉስጥ ገብተዋል። የሚቅጥለው ጥያቄ ይህን ፈተና እንዴት ማለፍ ይችላሉ? የሚለው ይሆናል።

የኦህዲድ ፈተናዎች ምንድናቸው?

ኦህዲድ በሁለት ተቀናቃኝ ኃይሎች (የኦሮሞ ሕዝባዊ ነቅናቄና ሕወሃት/ኢህአዲግ)  መካከል በመግባቱ የመጨረሻ ታሪካዊ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የተገደደበት ሁኔታ ውስት ይገኛል። እዚህ ላይ የሚደረገው ምርጫም ሆነ ውሳኔ ለድርጅቱ የመኖር ወይም ያለመኖር ውሳኔ ነው። ምን ማለት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት እላይ በተራ ቁጥር 1)A) እና B) ስር ወደ ተጠቀሱት ግምቶች መመለስ ያስፈልጋል።

  1. A) የሕወሃት/ኢህአዲግን ተልዕኮ ለማሳካት ተበሎ የሕዝቡን እንቅስቃሴ ለማቀዝቀዝ ከሆነ፤ አንደኛ የሕዝቡ ጥያቄ ካልተመለሰ እንቅስቃሴው ሊቀዘቅዝም ሊቆምም ስለማይችል፣ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኦሮሞ ሕዝብ መለየት ይሆናል። ሁለተኛ በተቃራኒው ተልዕኮውን ከግብ ማድረስ ካልቻለ፣ ከሕወሃት/ኢህአዲግ በኩል የሚደርስበት ውሳኔ ለድርጅቱም ሆነ ለአመራሩ አስጊ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።
  2. B) ወደ ሕዝባቸው ተመልሰው የሚቻላቸውን ለማድረግ ተገደው ከሆነ፣ በሕወሃት/ኢህአዲግ በኩል የፈለገውም እርምጃ ቢወሰድባቸው፣ ይህን አምነው ሊመጣ የሚችለውንም ተቀብለው ከሕዝቡ ጋር በመወገን የትግሉ አካል መሆን ነው።

2) የኦሮሞ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አስገድዶትም ይሁን ወይንም ደግሞ በፍላጎት ውስጣዊ ድርጅታዊ ተሃድሶ ለማድረገና ለሕዝቡ የቆመ ነፃ የፖለቲካ ድርጅት ለመሆን ከሆነ ደግሞ፤ የፈለገው መስዋዕት ቢያስከፍልም፣ ከሕዝቡ ጋር በመወገን በሀገሪቷ ሕገ መንግስት ላይ የተቀመጡትን መብቶች በመጠቀም የሕዝቡ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረግ።  ይህን በተግባር ካሳዩ፣ ለኦሮሞ ሕዝብ አንድ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ ለመውጣት ዕድል ይኖረዋል።

እንግዲህ ባጭሩ ለማጠቃለል፣ የኦህዲድ ትልቁ ፈተና ከላይ የተጠቀሱትን ዉሳኔዎች ተግባራዊ ማድረግ ላይ ነው።

ኦህዲድ እንደ አንድ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ ለመውጣትና በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተውዳጅነትን ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?

የኦሮሞ ሕዝብ ባሁኑ ጊዜ ከምንጊዜውም የበለጠ እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው። እዚህ ላይ ሁሉንም መዘርዘር ባይቻልም አንዳንድ ዋና ዋና የሆኑትን ችገሮች ለማንሳትና እንደ አንገብጋቢነታቸው ለማስቀመጥ፥

  • ) በኦሮሚያ ድንበር ላይ ጦርነት ተከፍቶበት ሕዝባችን ከቀን ወደ ቀን እየሞተና እየተፈናቀለ ይገኛል
  • ) በመላው ኦሮሚያ ሕዝባችን ሰላም አጥተው እየታመሱ ይገኛሉ
  • ) ዜጎቻችን በየ እስር ቤቶች በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ
  • ) ሕዝባችን ከቀዬው ተፈናቅለው፣ ኑሮአቸው ፈርሶ ለማኝ ሆነው በየመንገዱ ስንከራተቱ ይታያሉ

እንግዲህ ኦህዲድ ወይንም የድርጅቱ አዲሱ አመራር በየሄዱበት እንደ ማር የሚጣፍጥ አባባል ከመናገር፤ በየሄዱበት ቃል ኪዳን ከመግባት፤ ሕዝባችን ሰላም አጥተው አየተሰቃዩ በሚገኝበት ወቅት ስለ ኢኮኖሚ አብዮት ከማውራት፤ ቅድሚያ ማግኘት ላለበቸው አንግብጋቢ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ መስራት አለባቸው። ቢያንስ እላይ ከ ) እስክ ) የተዘረዘሩትን ችግሮች እንደ አስቸኳይነታቸው መፍትሄ እንዲያገኙ መስራት ግዴታ ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን ፈተናውን መውደቅ ይሆናል ማለት ነው። ያለፈው አልፏልና የሕዝባችንን ስቃይና መከራ መጋራት ጊዜው አሁን ነው። ይህ ካልሆነ ግን ከታሪክ ተጠያቂነት አይድኑም፤ የድርጅቱም ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው።

Leave a comment.

Your email address will not be published. Required fields are marked*

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.